Proverbs 5
ከአመንዝራነት መጠንቀቅ
1ልጄ ሆይ፤ ጥበቤን ልብ በል፤የማስተዋል ቃሌንም በጥሞና አድምጥ፤
2ይህም ልባምነትን ገንዘብ እንድታደርግ፣
ከንፈሮችህም ዕውቀትን እንዲጠብቁ ነው።
3የአመንዝራ ሴት ከንፈር ማር ያንጠባጥባልና፤
አንደበቷም ከቅቤ ይለሰልሳል፤
4በመጨረሻ ግን እንደ እሬት ትመርራለች፤
ሁለት አፍ እንዳለውም ስል ሰይፍ ትሆናለች።
5እግሮቿ ወደ ሞት ይወርዳሉ፤
ርምጃዎቿም በቀጥታ ወደ ሲኦል ▼
▼ወይም መቃብር
ያመራሉ።6ስለ ሕይወት መንገድ ደንታ የላትም፤
መንገዶቿ ዘወርዋራ ናቸው፤ ለእርሷ ግን አይታወቃትም።
7እንግዲህ፣ ልጆቼ ሆይ፤ አድምጡኝ፤
ከምነግራችሁ ቃል ፈቀቅ አትበሉ።
8መንገድህን ከእርሷ አርቅ፤
በደጃፏም አትለፍ፤
9ይኸውም ጕብዝናህን ለሌሎች፣
ዕድሜህንም ለጨካኞች እንዳትሰጥ ነው፤
10ባዕዳን በሀብትህ እንዳይፈነጥዙ፣
ልፋትህም የሌላውን ሰው ቤት እንዳያበለጽግ ነው።
11በዕድሜህ መጨረሻ ታቃሥታለህ፤
ሥጋህና ሰውነትህ ሲከዳህ።
12እንዲህም ትላለህ፤ “ምነው ተግሣጽን ጠላሁ!
ልቤስ ምነው መታረምን ናቀ!
13የመምህሮቼን ቃል አልሰማሁም፤
አሠልጣኞቼንም አላደመጥኋቸውም፤
14በመላው ጉባኤ ፊት፣
ወደ ፍጹም ጥፋት ተቃርቤአለሁ።”
15ከገዛ ማጠራቀሚያህ ውሃ፣
ከገዛ ጕድጓድህም የሚፈልቀውን ውሃ ጠጣ።
16ምንጮችህ ተርፈው ወደ ሜዳ፣
ወንዞችህስ ወደ አደባባይ ሊፈስሱ ይገባልን?
17ለአንተ ብቻ ይሁኑ፤
ባዕዳን አይጋሩህ።
18ምንጭህ ቡሩክ ይሁን፤
በልጅነት ሚስትህም ደስ ይበልህ።
19እርሷ እንደ ተወደደች ዋላ፣ እንደ ተዋበች ሚዳቋ ናት፤
ጡቶቿ ዘወትር ያርኩህ፤
ፍቅሯም ሁልጊዜ ይማርክህ።
20ልጄ ሆይ፤ በአመንዝራ ሴት ፍቅር ለምን ትሰክራለህ?
የሌላዪቱንስ ሴት ብብት ስለ ምን ታቅፋለህ?
21የሰው መንገድ በእግዚአብሔር ፊት ግልጥ ነውና፤
እርሱ መሄጃውን ሁሉ ይመረምራል።
22ክፉውን ሰው የገዛ መጥፎ ሥራው ያጠምደዋል፤
የኀጢአቱም ገመድ ጠፍሮ ይይዘዋል።
23ከተግሣጽ ጕድለት የተነሣ ይሞታል፤
ከተላላነቱም ብዛት መንገድ ይስታል።
Copyright information for
AmhNASV