Proverbs 8
የጥበብ ጥሪ
1ጥበብ ጮኻ አትጣራምን?ማስተዋልስ ድምፅዋን ከፍ አድርጋ አታሰማምን?
2በመንገድ አጠገብ ባሉ ኰረብቶች፣
መንገዶቹ በሚገናኙበትም ላይ ትቆማለች፤
3ወደ ከተማዪቱ በሚያስገቡት በሮች አጠገብ፣
በመግቢያዎቹ ላይ፣ ድምፅዋን ከፍ አድርጋ እንዲህ ስትል ትጮኻለች፤
4“ሰዎች ሆይ፤ የምጠራው እኮ እናንተን ነው፤
ለሰው ልጆች ሁሉ ድምፄን ከፍ አደርጋለሁ።
5እናንተ ብስለት የጐደላችሁ፤ ጠንቃቃነትን ገንዘብ አድርጉ፤
እናንተ ተላሎች፤ ማስተዋልን አትርፉ።
6የምናገረው ጠቃሚ ነገር ስላለኝ አድምጡኝ፤
ቀና ነገር ለመናገር ከንፈሮቼን እከፍታለሁ።
7አንደበቴ እውነትን ይናገራል፤
ከንፈሮቼ ክፋትን ይጸየፋሉና።
8ከአንደበቴ የሚወጡት ቃሎች ሁሉ ጽድቅ ናቸው፤
አንዳቸውም ጠማማና ግራ የሚያጋቡ አይደሉም።
9በጥልቅ ለሚያስተውሉ ሁሉም ቀና ናቸው፤
ዕውቀት ላላቸውም ስሕተት የለባቸውም።
10ከብር ይልቅ ምክሬን፣
ከንጹሕ ወርቅ ይልቅ ዕውቀትን ምረጡ፤
11ጥበብ ከቀይ ዕንይበልጥ ውድ ናትና፤
ከምትመኙት ነገር ሁሉ አንዳች የሚስተካከላት የለም።
12“እኔ ጥበብ ከማስተዋል ጋር አብሬ እኖራለሁ፤
ዕውቀትና ልባምነት ገንዘቦቼ ናቸው።
13 እግዚአብሔርን መፍራት ክፋትን መጥላት ነው፤
እኔም ትዕቢትንና እብሪትን፣
ክፉ ጠባይንና ጠማማ ንግግርን እጠላለሁ።
14ምክርና ትክክለኛ ፍርድ የእኔ ናቸው፤
ማስተዋል አለኝ፤ ብርታት አለኝ።
15ነገሥታት በእኔ ይነግሣሉ፤
ገዦችም ትክክል የሆነውን ሕግ ይደነግጋሉ፤
16መሳፍንት በእኔ ይገዛሉ፤
በምድር ላይ የሚገዙ መኳንንትም ሁሉ በእኔ ያስተዳድራሉ። ▼
▼አያሌ የዕብራይስጥ ቅጆችና የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም፣ ብዙ የዕብራይስጥ ቅጆች በምድር ላይ በጽድቅ የሚገዙ ይላሉ።
17የሚወድዱኝን እወድዳቸዋለሁ፤
ተግተው የሚሹኝም ያገኙኛል።
18ሀብትና ክብር፣
ዘላቂ ብልጽግናና ስኬት በእኔ ዘንድ አሉ።
19ፍሬዬ ከንጹሕ ወርቅ ይበልጣል፤
ስጦታዬም ከነጠረ ብር።
20እኔ በጽድቅ መንገድ እሄዳለሁ፤
በፍትሕም ጐዳና እጓዛለሁ፤
21ለሚወድዱኝ ብልጽግና እሰጣለሁ፤
ግምጃ ቤታቸውንም እሞላለሁ።
22“እግዚአብሔር ከቀድሞ ሥራዎቹ በፊት፣
የተግባሮቹ ▼
▼ወይም የመንገዱ፣ የግዛቱ
መጀመሪያ አድርጎ አመጣኝ፤ ▼▼ወይም እግዚአብሔር በሥራው መጀመሪያ ያዘኝ ወይም እግዚአብሔር በሥራው መጀመሪያ አመጣኝ
23ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ፣
ከጥንት ከዘላለም ተሾምሁ። ▼
▼ወይም ተሠራ?
24ከውቅያኖሶች በፊት፣
የውሃ ምንጮች ከመፍለቃቸው በፊት ተወለድሁ፤
25ተራሮች ገና ሳይመሠረቱ፣
ከኰረብቶችም በፊት ተወለድሁ፤
26ምድርን ወይም ሜዳዎቿን፣
ወይም ምንም ዐይነት የዓለም ትቢያን ከመፍጠሩ በፊት እኔ ተወለድሁ።
27ሰማያትን በዘረጋ ጊዜ፣
በውቅያኖስ ላይ የአድማስ ምልክት ባደረገ ጊዜ እኔ እዚያ ነበርሁ፤
28ደመናትን በላይ ባጸና ጊዜ፣
የውቅያኖስን ምንጮች በመሠረተ ጊዜ፣
29ለባሕር ድንበርን በከለለ ጊዜ፣
ውሆችም የእርሱን ትእዛዝ እንዳያልፉ፣
የምድርንም መሠረቶች ወሰን ባበጀ ጊዜ፣
30በዚያን ጊዜ ከጐኑ ዋና ባለሙያ ነበርሁ።
ሁልጊዜ በፊቱ ሐሤት እያደረግሁ፣
ዕለት ተዕለት በደስታ እሞላ ነበር፤
31የእርሱ በሆነው መላው ዓለም ሐሤት እያደረግሁ፣
በሰው ልጆች ደስ እሰኝ ነበር።
32“እንግዲህ፣ ልጆቼ ሆይ፤ አድምጡኝ፤
መንገዴን የሚጠብቁ ቡሩካን ናቸው።
33ምክሬን አድምጡ፤ ጥበበኞች ሁኑ፤
ቸልም አትበሉት።
34በየዕለቱ ደጃፌ ላይ የሚጠብቅ፣
በበራፌ ላይ የሚጠባበቅ፣
የሚያዳምጠኝ ሰው ቡሩክ ነው።
35የሚያገኘኝ ሁሉ ሕይወትን ያገኛልና፤
ከእግዚአብሔርም ዘንድ ሞገስን ይቀበላል።
36የሚያጣኝ ሁሉ ግን ራሱ ይጐዳል፤
የሚጠሉኝም ሁሉ ሞትን ይወድዳሉ።”
Copyright information for
AmhNASV