Psalms 103
እግዚአብሔር ፍቅር ነው
የዳዊት መዝሙር።
1ነፍሴ ሆይ፤ እግዚአብሔርን ባርኪ፤የውስጥ ሰውነቴም ሁሉ ቅዱስ ስሙን ባርኪ።
2ነፍሴ ሆይ፤ እግዚአብሔርን ባርኪ፤
ውለታውንም ሁሉ አትርሺ፤
3ኀጢአትሽን ሁሉ ይቅር የሚል፣
ደዌሽንም ሁሉ የሚፈውስ፣
4ሕይወትሽን ከጥፋት ጕድጓድ የሚያድን፣
ምሕረትንና ርኅራኄን የሚያቀዳጅሽ፣
5ጕልማሳነትሽም እንደ ንስር ይታደስ ዘንድ፣
ምኞትሽን በበጎ ነገር የሚያረካ እርሱ ነው።
6 እግዚአብሔር ለተጨቈኑ ሁሉ፣
ቅን ፍርድንና ፍትሕን ይሰጣቸዋል።
7መንገዱን ለሙሴ፣
ሥራውንም ለእስራኤል ሕዝብ አሳወቀ።
8 እግዚአብሔር መሓሪና ይቅር ባይ፣
ለቍጣ የዘገየ፣ ፍቅሩም የበዛ ነው።
9እርሱ ሁልጊዜ በደልን አይከታተልም፤
ለዘላለምም አይቈጣም።
10እንደ ኀጢአታችን አልመለሰልንም፤
እንደ በደላችንም አልከፈለንም።
11ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፣
እንዲሁ ለሚፈሩት ምሕረቱ ታላቅ ናት።
12ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ፣
መተላለፋችንን በዚያው መጠን ከእኛ አስወገደ።
13አባት ለልጆቹ እንደሚራራ፣
እግዚአብሔር ለሚፈሩት እንዲሁ ይራራል።
14እርሱ አፈጣጠራችንን ያውቃልና፤
ትቢያ መሆናችንንም ያስባል።
15ሰው እኮ ዘመኑ እንደ ሣር ነው፤
እንደ ዱር አበባ ያቈጠቍጣል፤
16ነፋስ በነፈሰበት ጊዜ ግን ድራሹ ይጠፋል፤
ምልክቱም በቦታው አይገኝም።
17 የእግዚአብሔር ምሕረት ግን፣
ከዘላለም እስከ ዘላለም በሚፈሩት ላይ ነው፤
ጽድቁም እስከ ልጅ ልጅ ድረስ በላያቸው ይሆናል፤
18ኪዳኑን በሚጠብቁት ላይ፣
ትእዛዙንም ለመፈጸም በሚተጕት ላይ ይሆናል።
19 እግዚአብሔር ዙፋኑን በሰማይ አጽንቷል፤
መንግሥቱም ሁሉን ትገዛለች።
20እናንተ ለቃሉ የምትታዘዙ መላእክቱ፣
ትእዛዙንም የምትፈጽሙ እናንተ ኀያላን፤
እግዚአብሔርን ባርኩ።
21እናንተ ፈቃዱን የምትፈጽሙ አገልጋዮቹ፣
ሰራዊቱ ሁሉ፣ እግዚአብሔርን ባርኩ።
22እናንተ በግዛቱ ሁሉ የምትኖሩ፣
ፍጥረቱ ሁሉ፣ እግዚአብሔርን ባርኩ፤
ነፍሴ ሆይ፤ እግዚአብሔርን ባርኪ።
Copyright information for
AmhNASV