‏ Psalms 104

የፍጥረት መብት

1ነፍሴ ሆይ፤ እግዚአብሔርን ባርኪ፤
እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ አንተ እጅግ ታላቅ ነህ፤
ክብርንና ግርማን ለብሰሃል።
2ብርሃንን እንደ ሸማ ተጐናጽፈሃል፤
ሰማያትንም እንደ ድንኳን መጋረጃ ዘረጋህ፤
3የእልፍኝህን አግዳሚ በውሆች ላይ አኖርህ፤
ደመናትን ሠረገላህ አደረግህ፤
በነፋስ ክንፍ ትሄዳለህ።
4መላእክትህን
መልእክተኞቹን ወይም አገልጋዮቹን
መንፈስ፣
አገልጋዮችህንም የእሳት ነበልባል ታደርጋለህ።

5ለዘላለም እንዳትናወጥ፣
ምድርን በመሠረቷ ላይ አጸናሃት።
6በጥልቁ እንደ ልብስ ሸፈንሃት፤
ውሆችም ከተራሮች በላይ ቆሙ።
7በገሠጽሃቸው ጊዜ ግን ፈጥነው ሄዱ፤
የነጐድጓድህንም ድምፅ በሰሙ ጊዜ ሸሹ።
8በተራሮች ላይ ፈሰሱ፤
ወዳዘጋጀህላቸው ስፍራ፣
ወደ ሸለቆዎች ወረዱ።
9ተመልሰው ምድርን እንዳይሸፍኑ፣
ዐልፈውም እንዳይመጡ ድንበር አበጀህላቸው።

10ምንጮችን በሸለቆ ውስጥ እንዲሄዱ አደረግህ፤
በተራሮችም መካከል ይፈስሳሉ፤
11የዱር እንስሳትም ከዚያ ይጠጣሉ፤
የሜዳ አህዮችም ጥማቸውን ይቈርጣሉ።
12የሰማይ ወፎች ጎጇቸውን በወንዞቹ ዳር ይሠራሉ፤
በቅርንጫፎችም መካከል ይዘምራሉ።
13ከላይ ከእልፍኝህ ተራሮችህን ታጠጣለህ፤
ምድርም በሥራህ ፍሬ ትረካለች።
14ከምድር ምግብን ታወጣ ዘንድ፣
ለእንስሳት ሣርን፣
ለሰው ልጆች ሥራ ዕፀዋትን ታበቅላለህ፤
15የሰውን ልብ ደስ የሚያሰኝ ወይን፣
ፊቱን የሚያወዛ ዘይት፣
ልቡን የሚያበረታ እህል በዚህ ይገኛል።
16ደግሞም የእግዚአብሔር ዛፎች፣
እርሱ የተከላቸውም የሊባኖስ ዝግባዎች ጠጥተው ይረካሉ፤
17ወፎች ጎጇቸውን በዚያ ይሠራሉ፤
ሽመላ በጥዶቹ ውስጥ ማደሪያ ታገኛለች።
18ረጃጅሙ ተራራ የዋሊያ መኖሪያ፣
የዐለቱም ዋሻዎች የሽኮኮ መሸሸጊያ ናቸው።

19ጨረቃን የወቅቶች መለያ አደረግሃት፤
ፀሓይም የምትጠልቅበትን ጊዜ ታውቃለች።
20ጨለማን ታመጣለህ፤ ሌሊትም ይሆናል፤
የዱር አራዊትም ሁሉ በዚህ ጊዜ ወጥተው ይራወጣሉ።
21የአንበሳ ግልገሎች ምግብ ፍለጋ ይጮኻሉ፤
የሚበሉትንም ከእግዚአብሔር ይሻሉ።
22ፀሓይ በወጣች ጊዜም ይመለሳሉ፤
በየጐሬያቸውም ገብተው ይተኛሉ።
23ሰውም ወደ ሥራው ይሄዳል፤
እስኪመሽም በተግባሩ ላይ ይሰማራል።

24 እግዚአብሔር ሆይ፤ ሥራህ እንዴት ብዙ ነው!
ሁሉን በጥበብ ሠራህ፤
ምድርም በፍጥረትህ ተሞላች።
25ይህች ባሕር ሰፊና የተንጣለለች ናት፤
ታላላቅና ታናናሽ እንስሳት፣
ስፍር ቍጥር የሌላቸውም ነፍሳት በውስጧ አሉ።
26መርከቦች በላይዋ ይመላለሳሉ፤
አንተ የፈጠርኸውም ሌዋታን በውስጧ ይፈነጫል።

27ምግባቸውን በወቅቱ ትሰጣቸው ዘንድ፣
እነዚህ ሁሉ አንተን ተስፋ ያደርጋሉ።
28በሰጠሃቸውም ጊዜ፣
አንድ ላይ ያከማቻሉ፤
እጅህንም ስትዘረጋ፣
በመልካም ነገር ይጠግባሉ።
29ፊትህን ስትሰውር፣
በድንጋጤ ይሞላሉ፤
እስትንፋሳቸውንም ስትወስድባቸው ይሞታሉ፤
ወደ ዐፈራቸውም ይመለሳሉ።
30መንፈስህን ስትልክ፣
እነርሱ ይፈጠራሉ፤
የምድርንም ገጽ ታድሳለህ።
31 የእግዚአብሔር ክብር ለዘላለም ጸንቶ ይኑር፤
እግዚአብሔር በሥራው ደስ ይበለው፤
32እርሱ ምድርን ሲመለከት፣ ትንቀጠቀጣለች፤
ተራሮችም እርሱ ሲዳስሳቸው ይጤሳሉ።

33በሕይወት ሳለሁ ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ፤
ቆሜ እስከ ሄድሁ ድረስም አምላኬን እወድሳለሁ።
34እኔ በእግዚአብሔር ደስ እንደሚለኝ፣
የልቤ ሐሳብ እርሱን ደስ ያሰኘው።
35ኀጥኣን ከምድር ገጽ ይጥፉ፤
ዐመፀኞች ከእንግዲህ አይገኙ።

ነፍሴ ሆይ፤ እግዚአብሔርን ባርኪ፤
ሃሌ ሉያ።
እግዚአብሔር ይመስገን የሚሉ ትርጕሞች አሉ፤ በሰብዓ ሊቃናት ትርጕም ይህ መሥመር በመዝ 105 መጀመሪያ ላይ ይገኛል።

Copyright information for AmhNASV