‏ Psalms 108

የጧት ውዳሴና ብሔራዊ ጸሎት

108፥1-5 ተጓ ምብ – መዝ 57፥7-11 108፥6-13 ተጓ ምብ – መዝ 60፥5-12

የዳዊት መዝሙር፤ ማሕሌት።

1አምላክ ሆይ፤ ልቤ ጽኑ ነው፤
እዘምራለሁ፤ በፍጹም ነፍሴም እዘምራለሁ።
2በገናም መሰንቆም ተነሡ፤
እኔም ማልጄ እነሣለሁ።
3 እግዚአብሔር ሆይ፤ በሕዝብ መካከል አመሰግንሃለሁ፤
በሕዝቦችም መካከል እዘምርልሃለሁ።
4ምሕረትህ ከሰማያት በላይ ታላቅ ናትና፤
ታማኝነትህም እስከ ጠፈር ትደርሳለች።
5አምላክ ሆይ፤ ከሰማያት በላይ ከፍ ከፍ በል፤
ክብርህም በምድር ሁሉ ላይ ትንሰራፋ።

6ወዳጆችህ ይድኑ ዘንድ፣
በቀኝ እጅህ ታደግ፤ መልስልኝም።
7እግዚአብሔር ከመቅደሱ እንዲህ አለ፤
ደስ እያለኝ ሴኬምን እሸነሽናለሁ፤
“የሱኮትንም ሸለቆ እለካለሁ።
8ገለዓድ የእኔ ነው፤ ምናሴም የእኔ ነው፤
ኤፍሬም የራስ ቍሬ ነው፤
ይሁዳም በትረ መንግሥቴ።
9ሞዓብ መታጠቢያ ገንዳዬ ነው፤
በኤዶምያስ ላይ ጫማዬን እወረውራለሁ፤
በፍልስጥኤም ላይ በድል አድራጊነት እፎክራለሁ።”

10ወደ ተመሸገችው ከተማ ማን ይወስደኛል?
ወደ ኤዶምያስስ ማን ያደርሰኛል?
11እግዚአብሔር ሆይ፤ የጣልኸን አንተ አይደለህምን?
አምላክ ሆይ፤ ከሰራዊታችንም ጋር አልወጣ አልህ!
12አሁንም የሰው ማዳን ከንቱ ነውና፣
በጠላታችን ላይ ድልን አቀዳጀን።
13እግዚአብሔር ሲረዳን ብርቱ እንሆናለን፤
ጠላቶቻችንንም ከእግሩ በታች የሚረግጥ እርሱ ነው።
Copyright information for AmhNASV