‏ Psalms 113

ለታላቁና ለመሓሪው ጌታ ምስጋና

1ሃሌ ሉያ።
እግዚአብሔር ይመስገን ማለት ሲሆን፣ በ9 ላይም ይገኛል።


የእግዚአብሔር አገልጋዮች ሆይ፤ አመስግኑት፤
የእግዚአብሔርን ስም አወድሱ።
2ከአሁን እስከ ዘላለም፣
የእግዚአብሔር ስም የተመሰገነ ይሁን።
3ከፀሓይ መውጫ እስከ መግቢያው ድረስ፣
የእግዚአብሔር ስም የተመሰገነ ይሁን።

4 እግዚአብሔር ከሕዝቦች ሁሉ በላይ ከፍ ያለ ነው፤
ክብሩም ከሰማያት በላይ ነው።
5እንደ አምላካችን እንደ እግዚአብሔር
በላይ በዙፋኑ የተቀመጠ ማን ነው?
6በሰማይና በምድር ያሉትንስ ለማየት፣
ራሱን ወደ ታች ዝቅ የሚያደርግ ማን ነው?

7ድኻውን ከትቢያ ያነሣል፤
ችግረኛውን ከዐመድ ከፍ ከፍ ያደርጋል፤
8ከመኳንንትም እኩል ስፍራ ይሰጠዋል፤
ከሕዝቡም ሹማምት ጋር ያስቀምጠዋል።
9መካኒቱን ሴት በቤት ያኖራታል፤
ደስተኛም የልጆች እናት ያደርጋታል።

ሃሌ ሉያ።
Copyright information for AmhNASV