Psalms 137
የግዞተኞች ቅኔ
1በባቢሎን ወንዞች አጠገብ፣ በዚያ ተቀምጠን ሳለን፣ጽዮን ትዝ ባለችን ጊዜ አለቀስን።
2እዚያም በአኻያ ዛፎች ላይ፣
በገናዎቻችንን ሰቀልን።
3የማረኩን በዚያ እንድንዘምርላቸው ጠየቁን፤
የሚያሠቃዩን የደስታ ዜማ ፈለጉብን፤
ደግሞም፣ “ከጽዮን መዝሙሮች አንዱን ዘምሩልን” አሉን።
4 የእግዚአብሔርን ዝማሬ፣
እንዴት በባዕድ ምድር እንዘምር!
5ኢየሩሳሌም ሆይ፤ ብረሳሽ፣
ቀኝ እጄ ትክዳኝ።
6ሳላስታውስሽ ብቀር፣
ኢየሩሳሌምን የደስታዬ ቍንጮ ባላደርግ፣
ምላሴ ከትናጋዬ ጋር ትጣበቅ።
7 እግዚአብሔር ሆይ፤ ኢየሩሳሌም በወደቀችበት ቀን፣
ኤዶማውያን እንዴት እንደ ዛቱ ዐስብ፤
ደግሞም፣ “አፍርሷት፤
ፈጽማችሁ አፈራርሷት!” አሉ።
8አንቺ አጥፊ የሆንሽ የባቢሎን ልጅ ሆይ፤
በእኛ ላይ ስለ ፈጸምሽው ድርጊት፣
የእጅሽን የሚሰጥሽ የተመሰገነ ነው፤
9ሕፃናትሽንም ይዞ፣
በዐለት ላይ የሚፈጠፍጥ የተመሰገነ ነው።
Copyright information for
AmhNASV