‏ Psalms 138

የምስጋና መዝሙር

የዳዊት መዝሙር።

1እግዚአብሔር ሆይ፤ በፍጹም ልቤ አመሰግንሃለሁ፤
በአማልክት ፊት በመዝሙር አወድስሃለሁ።
2ወደ ቅዱስ መቅደስህ እሰግዳለሁ፤
ስለ ምሕረትህና ስለ ታማኝነትህ፣
ለስምህ ምስጋና አቀርባለሁ፤
ስምህንና ቃልህን፣
ከሁሉ በላይ ከፍ ከፍ አድርገሃልና።
3በጠራሁህ ቀን መልስ ሰጠኸኝ፤
ነፍሴን በማደፋፈርም ብርቱ አደረግኸኝ።

4 እግዚአብሔር ሆይ፤ የአፍህን ቃል በሰሙ ጊዜ፣
የምድር ነገሥታት ሁሉ ያመስግኑህ።
5 የእግዚአብሔር ክብር ታላቅ ነውና፣
ስለ እግዚአብሔር መንገድ ይዘምሩ።

6 እግዚአብሔር በከፍታ ስፍራ ቢሆንም፣ ዝቅ ያለውን ይመለከተዋል፤
ትዕቢተኛውን ከሩቅ ያውቀዋል።
7በመከራ መካከል ብሄድም፣
አንተ ሕይወቴን ትጠብቃታለህ፤
በጠላቶቼ ቍጣ ላይ እጅህን ትዘረጋለህ፤
በቀኝ እጅህም ታድነኛለህ።
8 እግዚአብሔር በእኔ ላይ ያለውን ዐላማ ይፈጽማል፤
እግዚአብሔር ሆይ፤ ምሕረትህ ለዘላለም ነው።
የእጅህንም ሥራ ቸል አትበል።
Copyright information for AmhNASV