‏ Psalms 140

በክፉዎች ላይ የቀረበ ጸሎት

ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር።

1 እግዚአብሔር ሆይ፤ ከክፉ ሰዎች አድነኝ፤
ከዐመፀኞችም ሰዎች ጠብቀኝ፤
2እነርሱ በልባቸው ክፉ ነገር ያውጠነጥናሉ፤
በየዕለቱም ጦርነት ይጭራሉ።
3ምላሳቸውን እንደ እባብ ያሾላሉ፤
ከከንፈራቸውም በታች የእፉኝት መርዝ አለ። ሴላ

4 እግዚአብሔር ሆይ፤ ከክፉዎች እጅ ጠብቀኝ፤
እግሮቼንም ለመጥለፍ ከሚያደቡ ዐመፀኞች ሰውረኝ።
5ትዕቢተኞች ወጥመድ በስውር አስቀመጡብኝ፤
የመረባቸውን ገመድ ዘረጉብኝ፤
በመንገዴም ላይ አሽክላ አኖሩ። ሴላ

6 እግዚአብሔር ሆይ፤ “አንተ አምላኬ ነህ” እልሃለሁ፤
እግዚአብሔር ሆይ፤ የልመና ጩኸቴን ስማ።
7ብርቱ አዳኝ የሆንህ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤
በጦርነት ዕለት የራስ ቍር ሆንኸኝ።
8 እግዚአብሔር ሆይ፤ የክፉዎች ምኞት አይፈጸም፤
በትዕቢትም እንዳይኵራሩ፣
ዕቅዳቸው አይሳካ። ሴላ

9ዙሪያዬን የከበቡኝ ሰዎች ራስ፣
የከንፈራቸው መዘዝ ይጠምጠምበት።
10የእሳት ፍም በላያቸው ይውረድ፤
ዳግመኛም እንዳይነሡ ወደ እሳት ይጣሉ፤
ማጥ ወዳለበት ጕድጓድ ይውደቁ።
11ምላሰኛ በምድሪቱ ጸንቶ አይኑር፤
ዐመፀኛውን ሰው ክፋት አሳድዶ ያጥፋው።

12 እግዚአብሔር ለድኻ ፍትሕን እንደሚያስከብር፣
ለችግረኛውም ትክክለኛ ፍርድን እንደሚሰጥ ዐውቃለሁ።
13ጻድቃን በእውነት ስምህን ያመሰግናሉ፤
ቅኖችም በፊትህ ይኖራሉ።
Copyright information for AmhNASV