Psalms 146
ለረድኤት አምላክ ምስጋና
1ሃሌ ሉያ። ▼▼አንዳንዶች ከቍጥር 10 ጭምር እግዚአብሔር ይመስገን ይላሉ።
ነፍሴ ሆይ፤ እግዚአብሔርን ባርኪ።
2በምኖርበት ዘመን ሁሉ እግዚአብሔርን
አመሰግናለሁ፤
በሕይወትም እስካለሁ ለአምላኬ እዘምራለሁ።
3በገዦች አትታመኑ፤ ማዳን በማይችሉ ሥጋ ለባሾችም አትመኩ።
4መንፈሳቸው ትወጣለች፤ ወደ መሬታቸውም ይመለሳሉ፤
ያን ጊዜም ዕቅዳቸው እንዳልነበር ይሆናል።
5ረዳቱ የያዕቆብ አምላክ የሆነ፣
ተስፋውንም በአምላኩ በእግዚአብሔር ላይ የጣለ ሰው ምስጉን ነው፤
6እርሱ ሰማይንና ምድርን፣ ባሕርንም፣
በእነዚህም ውስጥ ያለውን ሁሉ የፈጠረ፣
ታማኝነቱንም ለዘላለም የሚጠብቅ ነው፤
7ለተበደሉት የሚፈርድ፣
ለተራቡት ምግብን የሚሰጥ እርሱ ነው፤
እግዚአብሔር እስረኞችን ከእስራት ያወጣል፤
8 እግዚአብሔር የዕውራንን ዐይን ያበራል፤
እግዚአብሔር የተዋረዱትን ከፍ ያደርጋል፤
እግዚአብሔር ጻድቃንን ይወድዳል፤
9 እግዚአብሔር ስደተኞችን ይጠብቃል፤
ድኻ ዐደጎችንና መበለቶችን ይደግፋል፤
የክፉዎችን መንገድ ግን ያጠፋል።
10 እግዚአብሔር ለዘላለም ይነግሣል፤
ጽዮን ሆይ፤ አምላክሽ ለትውልድ ሁሉ ንጉሥ ነው።
ሃሌ ሉያ።
Copyright information for
AmhNASV