Psalms 31

የመከራ ጊዜ ጸሎት

31፥1-4 ተጓ ምብ – መዝ 71፥1-3

ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር።

1 እግዚአብሔር ሆይ፤ በአንተ ተተግኛለሁ፤
እንግዲህ ዕፍረት ከቶ አይድረስብኝ፤
በጽድቅህም ታደገኝ።
2ጆሮህን ወደ እኔ መልሰህ ስማኝ፤
ፈጥነህ አድነኝ፤
መጠጊያ ዐለት ሁነኝ፤
ታድነኝም ዘንድ ምሽግ ሁነኝ።
3አንተ ዐለቴና መጠጊያዬ ነህና፣
ስለ ስምህ ስትል ምራኝ፤
መንገዱንም ጠቍመኝ።
4አንተ መጠጊያዬ ነህና፣
በስውር ከተዘረጋብኝ ወጥመድ አውጣኝ።
5መንፈሴን በእጅህ ዐደራ እሰጣለሁ፤
እግዚአብሔር የእውነት አምላክ ሆይ፤
አንተ ተቤዠኝ።

6ለከንቱ ጣዖታት ስፍራ የሚሰጡትን ጠላሁ፤
ነገር ግን በእግዚአብሔር ታመንሁ።
7በምሕረትህ ደስ እሰኛለሁ፤ ሐሤትም አደርጋለሁ፤
መከራዬን አይተሃልና፤
የነፍሴንም ጭንቀት ዐውቀሃል።
8ለጠላት አሳልፈህ አልሰጠኸኝም፤
ነገር ግን እግሮቼን ሰፊ ቦታ ላይ አቆምሃቸው።

9 እግዚአብሔር ሆይ፤ በመከራ ውስጥ ነኝና ማረኝ፤
ዐይኖቼ በሐዘን ደክመዋል፤
ነፍስና ሥጋዬም ዝለዋል።
10ሕይወቴ በመጨነቅ፣
ዕድሜዬም በመቃተት ዐለቀ፤
ከመከራዬ
ወይም ከበደሌ
የተነሣ ጕልበት ከዳኝ፤
ዐጥንቴም በውስጤ ሟሟ።
11ከጠላቶቼ ሁሉ የተነሣ፣
ለጎረቤቶቼ መዘባበቻ፣
ለወዳጆቼ መሣለቂያ ሆኛለሁ፤
መንገድ ላይ የሚያገኙኝም ይሸሹኛል።
12እንደ ሞተ ሰው ተረሳሁ፤
እንደ ተሰበረ የሸክላ ዕቃም ተቈጠርሁ።
13የብዙ ሰዎችን ሹክሹክታ እሰማለሁና፤
ዙሪያው ሁሉ ሽብር አለ፤
በእኔ ላይ ባሤሩ ጊዜ፣
ሕይወቴን ለማጥፋት ዶለቱ።

14 እግዚአብሔር ሆይ፤ እኔ ግን በአንተ እታመናለሁ፤
“አንተ አምላኬ ነህ” እልሃለሁም።
15ዘመኔ ያለው በእጅህ ነው፤
ከጠላቶቼ እጅ ታደገኝ፤
ከሚያሳድዱኝም አድነኝ።
16ፊትህን በአገልጋይህ ላይ አብራ፤
በምሕረትህም አድነኝ።
17 እግዚአብሔር ሆይ፤
ወደ አንተ እጮኻለሁና አልፈር፤
ክፉዎች ግን ይፈሩ፤
ሲኦል
ወይም መቃብር
ገብተውም ጸጥ ይበሉ።
18በጻድቁ ላይ በእብሪት የሚናገሩ፣
ትዕቢትንና ንቀትን የተሞሉ፣
ዋሾ ከንፈሮች ድዳ ይሁኑ።

19በሰዎች ልጆች ፊት፣
ለሚፈሩህ ያስቀመጥሃት፣
መጠጊያ ላደረጉህም ያዘጋጀሃት፣
በጎነትህ ምንኛ በዛች!
20ከሰዎች ሤራ፣
በማደሪያህ ውስጥ ትሸሽጋቸዋለህ፤
ከአንደበት ጭቅጭቅም፣
በድንኳንህ ውስጥ ትከልላቸዋለህ።

21በተከበበች ከተማ ውስጥ፣
የሚያስደንቅ ምሕረቱን ያሳየኝ፣
እግዚአብሔር ይባረክ።
22እኔ በደነገጥሁ ጊዜ፣
“ከዐይንህ ፊት ተወግጃለሁ” አልሁ፤
አንተ ግን ወደ አንተ ስጮኽ፣
የልመናዬን ቃል ሰማህ።
23እናንተ ቅዱሳኑ ሁሉ፣ እግዚአብሔርን ውደዱት!
እግዚአብሔር ታማኞችን ይጠብቃል፤
ትዕቢተኞችን ግን ፈጽሞ ይበቀላቸዋል።
24 እግዚአብሔርን ተስፋ የምታደርጉ ሁሉ፤
በርቱ፤ ልባችሁም ይጽና።
Copyright information for AmhNASV