Psalms 53

አምላክ የለሾች

53፥1-6 ተጓ ምብ – መዝ 14፥1-7

ለመዘምራን አለቃ፤ በማኸላት፤ የዳዊት ትምህርት
ርእሱ ምናልባት የመዝሙሩን ሁኔታ የሚያሳይ ሊሆን ይችላል።

1ቂል በልቡ፣
“እግዚአብሔር የለም” ይላል።
ብልሹዎች ናቸው፤ ተግባራቸውም ጸያፍ ነው፤
በጎ ነገርን የሚያደርግ አንድ እንኳ የለም።

2በማስተዋል የሚመላለስ፣
እግዚአብሔርን የሚፈልግ እንዳለ ለማየት፣
እግዚአብሔር ከሰማይ
ወደ ሰው ልጆች ተመለከተ።
3ሁሉም ወደ ሌላ ዘወር አሉ፤
በአንድነትም ተበላሹ፤
አንድ እንኳ
በጎ የሚያደርግ የለም።

4ሰው እንጀራ እንደሚበላ ሕዝቤን የሚበሉት፣
እግዚአብሔርንም ጠርተው የማያውቁት፣
እነዚያ ክፉ አድራጊዎች ከቶ አይማሩምን?
5የሚያስፈራ ነገር በሌለበት፣
በዚያ፣ በፍርሀት ተዋጡ፤
እግዚአብሔር የዘመቱብህን ሰዎች ዐጥንት በተነ፤
እርሱ እግዚአብሔር ስለ ናቃቸው፣ አንተ አሳፈርሃቸው።

6ምነው ለእስራኤል የሚሆን መዳን ከጽዮን በወጣ!
እግዚአብሔር የሕዝቡን ምርኮ በሚመልስበት ጊዜ፣
ያዕቆብ ሐሤት ያድርግ፤ እስራኤል ደስ ይበለው።
Copyright information for AmhNASV