Psalms 85
ስለ ሰላም የቀረበ ጸሎት
ለመዘምራን አለቃ፤ የቆሬ ልጆች መዝሙር።
1 እግዚአብሔር ሆይ፤ ለምድርህ በጎ ውለሃል፤የያዕቆብንም ምርኮ መለስህ።
2የሕዝብህን በደል ይቅር አልህ፤
ኀጢአታቸውንም ሁሉ ሸፈንህ። ሴላ
3መዓትህን ሁሉ አራቅህ፤
ከብርቱ ቍጣህም ተመለስህ።
4መድኀኒታችን የሆንህ አምላክ ሆይ፤ መልሰን፤
በእኛ ላይ የተቃጣውን ቍጣህን መልሰው።
5የምትቈጣን ለዘላለም ነውን?
ቍጣህስ ከትውልድ እስከ ትውልድ ይቀጥላልን?
6ሕዝብህ በአንተ ሐሤት ያደርግ ዘንድ፣
መልሰህ ሕያዋን አታደርገንምን?
7 እግዚአብሔር ሆይ፤ ምሕረትህን አሳየን፤
ማዳንህን ለግሰን።
8 እግዚአብሔር አምላክ የሚናገረውን እሰማለሁ፤
ለሕዝቡ፣ ለቅዱሳኑ ሰላምን ይናገራልና፤
ዳሩ ግን ወደ ከንቱ ምግባራቸው አይመለሱ።
9ክብሩ በምድራችን ይኖር ዘንድ፣
ማዳኑ ለሚፈሩት በርግጥ ቅርብ ነው።
10ምሕረትና ታማኝነት ተገናኙ፤
ጽድቅና ሰላም ተቃቀፉ።
11ታማኝነት ከምድር በቀለች፤
ጽድቅም ከሰማይ ተመለከተች።
12 እግዚአብሔር በጎ ነገር ይለግሳል፤ ምድራችንም ፍሬዋን ትሰጣለች።
13ጽድቅ በፊቱ ይሄዳል፤
ለአረማመዱም መንገድ ያዘጋጃል።
Copyright information for
AmhNASV