‏ Psalms 69

እንጕርጕሮ

ለመዘምራን አለቃ፤ “በጽጌረዳ” ዜማ፤ የዳዊት መዝሙር።

1አምላክ ሆይ፤ አድነኝ፤
ውሃ እስከ ዐንገቴ ደርሶብኛልና።
2የእግር መቆሚያ በሌለው፣
በጥልቅ ረግረግ ውስጥ ሰጥሜአለሁ፤
ወደ ጥልቅ ውሃ ገባሁ፤
ሞገዱም አሰጠመኝ።
3በጩኸት ደከምሁ፤
ጉረሮዬም ደረቀ፤
አምላኬን በመጠባበቅ፣
ዐይኖቼ ፈዘዙ።
4ያለ ምክንያት የሚጠሉኝ፣
ከራሴ ጠጕር በዙ፤
ሕይወቴን ለማጥፋት የሚፈልጉ፣
በከንቱም የሚጠሉኝ ብዙዎች ሆኑ፤
ያልሰረቅሁትን ነገር፣
መልሰህ አምጣ ተባልሁ።

5እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ሞኝነቴን ታውቃለህ፤
በደሌም ከአንተ የተሰወረ አይደለም።
6ጌታ የሰራዊት አምላክ ሆይ፤
አንተን ተስፋ የሚያደርጉ፣
በእኔ ምክንያት አይፈሩ፤
የእስራኤል አምላክ ሆይ፤
አንተን አጥብቀው የሚሹ፣
ከእኔ የተነሣ አይዋረዱ።
7ስለ አንተ ስድብን ታግሻለሁና፤
ዕፍረትም ፊቴን ሸፍኗልና።
8ለወንድሞቼ እንደ ባዕድ፣
ለእናቴም ልጆች እንደ እንግዳ ሆንሁባቸው።
9የቤትህ ቅናት በላችኝ፤
የሚሰድቡህም ስድብ በላዬ ዐርፏል።
10ነፍሴን በጾም ባስመረርሁ ጊዜ፣
እነርሱ ሰደቡኝ።
11ማቅ በለበስሁ ጊዜ፣
መተረቻ አደረጉኝ።
12በቅጥሩ ደጅ ለሚቀመጡት የመነጋገሪያ ርእስ፣
ለሰካራሞችም መዝፈኛ ሆንሁ።

13 እግዚአብሔር ሆይ፤ እኔ ግን በወደድኸው ሰዓት፣
ወደ አንተ እጸልያለሁ፤
አምላክ ሆይ፤ በታላቅ ምሕረትህ፣
በማዳንህም ርግጠኝነት መልስልኝ።
14ከረግረግ አውጣኝ፤
እሰጥም ዘንድ አትተወኝ፤
ከጥልቅ ውሃ፣
ከእነዚያ ከሚጠሉኝ ታደገኝ።
15ጐርፍ አያጥለቅልቀኝ፤
ጥልቅ ውሃም አይዋጠኝ፤
ጕድጓዱም ተደርምሶ አይዘጋብኝ።

16 እግዚአብሔር ሆይ፤ ምሕረትህ በጎ ናትና ስማኝ፤
እንደ ርኅራኄም ብዛት መለስ በልልኝ።
17ፊትህን ከባሪያህ አትሰውር፤
ጭንቅ ውስጥ ነኝና ፈጥነህ መልስልኝ።
18ወደ እኔ ቀርበህ ታደገኝ፤
ስለ ጠላቶቼም ተቤዠኝ።

19የደረሰብኝን ስድብ፣ ዕፍረትና ውርደት ታውቃለህ፤
ጠላቶቼንም አንድ በአንድ ታውቃቸዋለህ።
20ስድብ ልቤን ጐድቶታል፤
ተስፋዬም ተሟጥጧል፤
አስተዛዛኝ ፈለግሁ፤ አላገኘሁምም፤
አጽናኝም ፈለግሁ፤ አንድም አልነበረም።
21ምግቤን ከሐሞት ቀላቀሉ፤
ለጥማቴም ሆምጣጤ ሰጡኝ።

22የቀረበላቸው ማእድ ወጥመድ ይሁንባቸው፤
ለማኅበራቸውም አሽክላ ይሁን።
23ዐይኖቻቸው እንዳያዩ ይጨልሙ፤
ጀርባቸውም ዘወትር ይጕበጥ።
24መዓትህን በላያቸው አፍስስ፤
የቍጣህም መቅሠፍት ድንገት ይድረስባቸው።
25ሰፈራቸው ባድማ ይሁን፤
በድንኳኖቻቸው የሚኖር አይገኝ፤
26አንተ የመታሃቸውን አሳድደዋልና፤
ያቈሰልሃቸውንም ሥቃያቸውን አባብሰዋል።
27በበደላቸው በደል ጨምርባቸው፤
ወደ ጽድቅህም አይግቡ።
28ከሕይወት መጽሐፍ ይደምሰሱ፤
ከጻድቃንም ጋር አይጻፉ።

29ነገር ግን እኔ በሥቃይና በጭንቅ ላይ እገኛለሁ፤
አምላክ ሆይ፤ ማዳንህ ደግፎ ይያዘኝ።

30የእግዚአብሔርን ስም በዝማሬ አወድሳለሁ፤
በምስጋናም ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ።
31ከበሬ ይልቅ፣
ቀንድና ጥፍር ካበቀለ እንቦሳ ይልቅ ይህ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋል።
32ድኾች ይህን ያያሉ፤ ደስም ይላቸዋል፤
እናንተ እግዚአብሔርን የምትሹ ልባችሁ ይለምልም!
33 እግዚአብሔር ችግረኞችን ይሰማልና፤
በእስራት ያለውንም ሕዝቡን አይንቅም።

34ሰማይና ምድር፣ ባሕርም፣
በውስጣቸውም የሚንቀሳቀስ ሁሉ ያመስግኑት።
35እግዚአብሔር ጽዮንን ያድናታልና፤
የይሁዳንም ከተሞች መልሶ ይሠራቸዋልና፤
ሕዝቡም በዚያ ይሰፍራል፤ ይወርሳታልም።
36የባሪያዎቹም ዘሮች ይወርሷታል፤
ስሙንም የሚወድዱ በዚያ ይኖራሉ።
Copyright information for AmhNASV